ለዓሣ ሀብት ልማት ዘርፍ ትልቅ አቅም የፈጠረው የንጋት ሐይቅ
መስከረም 26 ቀን 2018 ዓ.ም
ከታላቁ የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ጋር ተያይዞ የተፈጠረው የንጋት ሐይቅ ለዓሣ ሃብት ልማት ዘርፍ ምርታማነት ዕድገት ተጨማሪ ትልቅ አቅም የፈጠረ ሲሆን በዓመት እስከ 15 ሺህ ቶን ዓሣን የማምረት አቅም አለው።
ግብርና ሚኒስቴርም ይህንን የሃገር ሃብት የሆነውንና ለዓሣ ሃብት ልማት ዘርፍ ትልቅ አቅም የፈጠረውን የንጋት ሐይቅን በአግባቡ ለማስተዳደር፣ ለመጠቀም እንዲሁም ለዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠርና የምግብ ዋስትናችንን ለማረጋገጥ በተጨማሪም የግሉ ዘርፍ ባለሃብቶች በዘርፉ ላይ ተሰማርተው መስራት የሚችሉበትን ዕድል ለመፍጠር የሚያስችል የንጋት ሐይቅ የዓሣ ሃብት ልማት አጠቃቀም ረቂቅ መመሪያ አዘጋጅቷል።
በዛሬው ዕለትም ይህንን ረቂቅ መመሪያ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ የማስተቸትና መመሪያውን የሚያዳብሩ ሃሳቦችን ለማሰባሰብ የሚያስችል ዓውደ-ጥናት ተካሂዷል።
የዚህም ዓውደ-ጥናት ዋና ዓላማ በንጋት ሐይቅ እና በሌሎች የውሃ አካላት ውስጥ የሚገኙ የዓሣ ሃብቶቻችንን በዘላቂነትና ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማልማትና ለመቆጣጠር እንዲያስችል ረቂቅ መመሪያ ሰነዱን ለማዳበር የተሰጡ ምክረ-ሃሳቦችን በማካተት ስራ ላይ እንዲውል ለማድረግ ነው።



