ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን በአቡራሞ እና ዑራ ወረዳዎች ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገነባ እና የተለያዩ ቀበሌዎችን የሚያገናኝ የጠጠር መንገድ ፕሮጀክት መሰረተ ድንጋይ አስቀመጡ

(አሶሳ፣ ግንቦት 10/2016 ዓ.ም) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን በክልሉ አቡራሞ እና ዑራ ወረዳዎች ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገነባ እና የተለያዩ ቀበሌዎችን የሚያገናኝ የጠጠር መንገድ ፕሮጀክት መሰረተ ድንጋይ ዛሬ አስቀምጠዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ መንግስት የክልሉ ህዝቡ የሚያነሳቸውን የልማት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ በመፍታት የልማት ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል።

ባለፉት ዓመታት በፕሮጀክቶች ዘርፍ የሚስተዋለውን መጓተት ለማስቀረት የክልሉ መንግስት የወሰደውን ቁርጠኛ አመራር ጠቁመው፣ በዚህም ተጀምረው የሚጠናቀቁ እንጂ የሚጓተቱ ፕሮጀክቶች እንደማይኖሩ አቶ አሻድሊ ተናግረዋል።

በክልሉ ህብረተሰብ ዘንድ በተደጋጋሚ ሲነሳ ከነበሩት የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች መካከል አንዱ የመንገድ ጥያቄ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ጥያቄውንም መሰረት በማድረግ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ አካባቢዎችን በመለየት ደረጃ በደረጃ እየመለሱ ይገኛል ብለዋል።

የመንገድ መሰረተ ልማት የህዝቦችን የእርስ በእርስ የህዝብ ግንኙነት ከማጠናከር ባለፈ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ መስተጋብሮችን ለማጠናክር ፋይዳው የጎላ በመሆኑ፣ ባለፉት ዓመታት በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች ቀበሌን ከቀበሌ፣ ወረዳን ከወረዳ የሚያገናኙ እና ከክልሉ ዋና ከተማ ጋር የሚያስተሳስሩ በርካታ የመንገድ መሰረተ ልማቶችን ማከናወን መቻሉን ገልጸዋል።

የህዝቡን መሠረታዊ የልማት ጥያቄዎች በአግባቡ መመለስ የሚቻለው በአካባቢው ሰላም ሲኖር ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ህዝቡ ከምንም በላይ የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ የተጀመረውን የብልፅግና ጉዞ ከግብ ማድረስ እንዳለበትም አሳስበዋል።

የክልሉ የቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ የልማት ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ቶፊቅ አብዱልቀዩም፣ ፕሮጀክቱ በክልሉ መንግስት አቅም ሊሰሩ የማይችሉ ቁልፍ የልማት ጥያቄዎችን በመለየት እየመለሰ ነው ብለዋል።

በክልሉ በተለያዩ ወረዳዎች የተለያዩ መንገዶች፣ ት/ቤቶች፣ የጤና ተቋማትን እና መሰረተ ልማቶችን ተደራሽ በማድረግ አበረታች ማከናወኑን አስተባባሪው አብራርተዋል።

ዛሬ የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠለት የመንገድ ፕሮጀክት በቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ የልማት ፕሮጀክት የገንዘብ ድጋፍ እንደሚከናወንም አስረድተዋል።

የመንገድ ፕሮጀክቱ 43 ኪሜ ርዝመት ያለው ሲሆን፣ ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ በጀት በ18ወራት ተገንብቶ እንደሚጠናቀቅ መረዳት ተችሏል።

የመንገድ ፕሮጀክቱ በአሶሳ ዞን የአቡራሞ ወረዳ እና ዑራ ወረዳ ስድስት ቀበሌዎች የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ተገልጿል።

በፕሮግራሙ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን፣ በብልፅግና ፓርቲ ዋና መ/ቤት የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሙሳ አህመድ፣ የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኢሳቅ አብዱልቃድርን ጨምሮ የክልል፣ የዞን እና የወረዳ አመራሮች ተገኝተዋል ሲል የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ዘግቧል፤

+5

All reactions:

3Senbeta Kejela Moti, የቤ/ጉ/ክ/መ/ግብርና ቢሮ and 1 other

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *