በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች የእንስሳት ክትባት ዘመቻ ለማካሄድ ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ
*****************
(አሶሳ፣ ኅዳር 10/2018 ዓ/ም) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሁሉም አካባቢዎች የእንስሳት ክትባት ዘመቻ ለማካሄድ ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ።
በቢሮው የእንስሳትና አሳ ሀብት ልማት ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ብርሃኑ ኢትቻ (ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ፤ በ2018 በጀት ዓመት የሚሰጠውን የእንስሳት ክትባት በቀጣዮቹ ቀናት በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች ለመስጠት ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።
በክልሉ የእንስሳት ምርታማነትን ለማሳደግ ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ በየዓመቱ የእንስሳት በሽታን መከላከል የሚያስችል የክትባት አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን ጠቅሰው፣ በዚህም አበረታች ውጤት መገኘቱን አስረድተዋል።
ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የክትባት ዘመቻዎች በወረርሽን መልክ የሚከሰቱ የእንስሳት በሽታዎች የቀነሱ ሲሆን የእንስሳት ምርታማነት መጨመሩንም ነው ብርሃኑ ኢትቻ (ዶ/ር) የተናገሩት፡፡
የእንስሳት በሽታን አክሞ ከማዳን ይልቅ በመከላከሉ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ በመሆኑን የተናገሩት ምክትል ኃላፊው፣ በተያዘው በጀት ዓመትም ክትባቱ በአሶሳ፣ መተከል እና ካማሺ ዞኖች እንዲሁም በማኦና ኮሞ ልዩ ወረዳ በሁሉም ቀበሌዎች የሚሰጥ ሲሆን፣ ክትባቱን ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን አንስተዋል።
በተለያዩ ምክንያቶች ክትባቱ ከማይሰጣቸው እንስሳት ውጪ ያሉት 90 በመቶ የሚሆኑት እንስሳት እንደሚከተቡ ተናግረው፣ በዘመቻውም አምስት ዓይነት ክትባት እንደሚሰጥ አስረድተዋል፡፡
ሰሞኑን በሚጀመረው እና ለ10 ቀናት በሚካሄደው የክትባት ዘመቻ ከ484 ሺህ የዳልጋ ከብቶች፣ 491 ሺህ በላይ ፍየሎች እና በጎች፣ 1 ሚሊዮን ዶሮዎች፣ 21 ሺህ ለሚሆኑ ውሻዎች የእብደት መከላከያ ክትባት እንደሚሰጥም ጠቁመዋል፡፡
የክትባት ዘመቻውን የሚያስተባብሩ ባለሙያዎች መዘጋጀታቸውን ጠቅሰው፣ አርሶ-አደሩ መከተብ የሚገባቸውን ሁሉንም እንስሳቱን በወቅቱ ይዞ በመቅረብ እንዲያስከትብ አሳስበዋል፡፡
በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች እና ባለድርሻ አካላት ለክትባት ዘመቻው መሳካት የተለዬ ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
