በክልሉ ባለፉት ዓመታት የተተከሉ ችግኞች የአካባቢ ሥነ ምህዳርን ከማሻሻል ባለፈ የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያረጋገጡ ነው ‎***************

በክልሉ ባለፉት ዓመታት የተተከሉ ችግኞች የአካባቢ ሥነ ምህዳርን ከማሻሻል ባለፈ የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያረጋገጡ ነው
‎***************
(አሶሳ፣ ጥቅምት 27/2018 ዓ.ም) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባለፉት ዓመታት የተተከሉ ችግኞች የአከባባ ሥነ ምህዳርን ከማሻሻል ባለፈ የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያረጋገጡ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ።
‎የክልሉ ግብርና ቢሮ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃ እና አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ ፈቃዱ ደሳለኝ፣ በክልሉ ከ2011 ጀምሮ በተከናወነ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከግማሽ ቢሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውን ገልጸዋል።
የተተከሉት ችግኞችን የጽድቀት መጠን ለማረጋገጥ በዓመት ሁለት ጊዜ ቆጠራ እንደሚካሄድ ያነሱት ዳይሬክተሩ፣ ባለፉት ዓመታት ከተተከሉት ችግኞች ውስጥ ከ72 በመቶ በላይ የሚሆኑት መጽደቃቸውን ጠቁመዋል፡፡
‎በክልሉ ባለፉት ዓመታት የተተከሉ ችግኞች የአካባቢ ሥነ ምህዳርን ከማሻሻል ባለፈ የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በማሳደግ ረገድ ተጨባጭ ውጤት አስገኝተዋል ብለዋል፡፡
በመርሃ-ግብሩ የደን ሽፋንን ከመሳደግ ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው በርካታ ችግኞች በክላስተር መተከላቸውን ጠቁመው፣ ይህም የፍራፍሬ ምርቶችን ጨምሮ ወደ ገበያ የሚቀርበውን የግብርና ምርት እንዲጨምር አድርጓል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የተተከሉ ችግኞች ለንብ ማነብ ሥራ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር አርሶ አደሩ ከማር ምርት የሚያገኘው ጥቅም እንዲጨምር ትልቅ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኝም ነው ዳይሬክተሩ የጠቀሱት፡፡
መርሃ-ግብሩን ከተፋሰስ ልማት ጋር በማጣመር እየተሠራ እንደሚገኝ አንስተው፣ በዚህም ቀደም ሲል የተጎዱ አካባቢዎች እንዲያገግሙ በማድረግ የደረቁ ምንጮች እየለመለሙ መምጣታቸውን አስረድተዋል፡፡
በአረንጓደ አሻራ መርሃ-ግብር ባለቤት ያላቸው ችግኞችን የመትከል ልምድ ማዳበር ተችሏል ያሉት አቶ ፈቃዱ፣ የህብረተሰቡ ችግኞችን የመንከባከብ ባህል እየተሻሻለ መምጣቱን አመልክተዋል፡፡
ችግኞችን በመትከል ላይ እየተደረገ ያለውን ተነሳሽነት በእንክብካቤው ላይም በማስቀጠል በመጪው የበጋ ወቅት ችግኞችን ከእንስሳት እና ከሰው ንክኪ እንዲሁም ከሰደድ እሳት መጠበቅ እንደሚገባ አቶ ፈቃዱ ተናግረዋል፡፡
‎የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *