በክልሉ ከለውጡ ወዲህ በግብርናው ዘርፍ ያለውን ምቹ አቅም በመጠቀም በተሰሩ ሥራዎች አበረታች ውጤት ተገኝቷል፦ አቶ አሻድሊ ሀሰን
*************
(አሶሳ፣ ኅዳር 07/2018 ዓ.ም) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከለውጡ ወዲህ በግብርናው ዘርፍ ያለውን ምቹ አቅም በመጠቀም በተሰሩ ሥራዎች አበረታች ወጤት መገኘቱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ገለጹ።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ክልላዊ የ2017/18 የምርት ዘመን የአርሶ አደሮች የመስክ በዓል በባምባሲ ወረዳ አካሂዷል።
በወረዳው አያንቱ ቀበሌ በ29 ሺህ 500 ሄክታር መሬት እየለማ የሚገኝ የሊሙ እና 661 የቦቆሎ ዘር ብዜት ክላስተር፣ በቀሽማንዶ ቀበሌ በ59 ሄክታር መሬት ላይ እየለማ የሚገኝ አሶሳ-1 የማሽላ ዘር ብዜት እንዲሁም በመንደር 40 ቀበሌ በ40 ሄክታር ላይ እየለማ የሚገኝ የሩዝ ማሣዎችን ምልከታ ተደርጓል።
በመርሃ-ግብሩ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን፣ ለውጡን ተከትሎ በክልሉ በግብርናው ዘርፍ ያለውን ምቹ አቅም በመጠቀም በተሰሩ ሥራዎች አበረታች ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል።
በክልሉ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ጠቁመው፣ በግብርና ኢኒሼቲቮች የእንስሳት ሀብቶቻችን ወደመጠቀም ተሸጋግረናል ብለዋል።
የገጠር ትራንስፎርሜሽን ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተደረገ መሆኑን የጠቀሱት አቶ አሻድሊ፣ በዚህም የግብርና ምርታማነት ከመጨመር ባለፈ የገጠሩን ማኅበረሰብ ሕይወት ለማሻሻል እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
ክልሉ ለሩዝ ምርት አመቺ መሆኑን የተናገሩት አሻድሊ፣ ለዚህም በምርት ዘመኑ የተሠራው ሥራ ትልቅ ማሣያ በመሆኑ በቀጣይ ሩዝን ጨምሮ የቅባት እህሎችን በስፋት ለማምረት መሥራት ይገባል ብለዋል።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ባበክር ኻሊፋ፣ በ2017/18 የምርት ዘመን ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር በላይ ማሣ በዘር መሸፈኑን ገልጸው፣ 56 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚሰበሰብ ጠቁመዋል።
በምርት ዘመኑ የታረሰው መሬት ካለፈው የምርት ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ400 ሺህ ሄክታር መሬት ዕድገት አሳይቷል ብለዋል።
በምርት ዘመኑ 355 ሺህ 335 ሄክታር መሬቱ በክላስተር መልማቱንም አቶ ባበክር አንስተዋል።
የባምባሲ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱልዋህድ አዙቤር፣ በወረዳው በግብርናው ዘርፍ አበረታች ሥራ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው፣ በተያዘው የምርት ዘመን 8 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይጠበቃል ብለዋል።
በወረዳው መሣቸውን በክላስተር ያለሙ አርሶ አደሮች በበኩላቸው፣ ከስልጠና ጀምሮ ተከታታይ ድጋፍና ክትትል ማግኘታቸው ውጤታማ እንዳደረጋቸው ተናግረው፣ በቀጣይ የተሻለ ለመሥራት ዕቅድ እንዳላቸውም ተናግረዋል።

