በክልሉ የሜካናይዜሽን እርሻን በማስፋፋት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው-ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን
አሶሳ፤ህዳር 7/2018 (ኢዜአ)፦በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሜካናይዜሽን እርሻን በማስፋፋት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ተናገሩ።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግብርና ቢሮ ያዘጋጀው የአርሶ አደሮች የመስክ ቀን ጉብኝት በባምባሲ ወረዳ ተካሂዷል።
የመስክ ቀን ተሳታፊዎችም በወረዳው በተለያዩ ቀበሌዎች በኩታገጠም እየለሙ ያሉ የበቆሎ፣ ማሽላ እና ሩዝ ሰብሎችን ተመልክተዋል።
በመስክ ምልከታው ላይ የተገኙት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን እንደተናገሩት፤ በክልሉ የሜካናይዜሽን እርሻን በመተግበር እየተከናወነ የሚገኘው የግብርና ሥራ ውጤት እያስገኘ ነው።
አርሶ አደሩ የተሻሻሉ የሰብል አይነቶች በማልማት የምግብ ዋስትናውን ከማረጋገጥ በተጨማሪ የገቢ ምንጭ በሚያስገኙና ለኢንዱስትሪ ግብዓት በሚሆኑ ሰብሎች ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለበት ተናግረዋል።
በተለይ የክልሉ ስነ ምህዳር ለሩዝ ልማት ተስማሚ መሆኑን የተናገሩት አቶ አሻድሊ ሩዝ በክልሉ በተለያዩ ወረዳዎች በስፋት እየተመረተ መሆኑን ተናግረዋል።
የገጠር ትራንስፎርሜሽን እሳቤን በመተግበር የአርሶ አደሩን ኑሮ ለማሻሻልና ገቢውን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ባበክር ኃሊፋ በበኩላቸው እንዳሉት፤ በዘንድሮው የምርት ዘመን ከተለያዩ የሰብል አይነቶች 56 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል።
በክልሉ በ2017 የመኸር እርሻ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች መሸፈኑን ገልጸው፣ከእዚህ ውስጥ ከ750 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነው በማሽላና በቆሎ የለማ መሆኑን ተናግረዋል።
አርሶ አደሩ በኩታገጠም እርሻ ተሳትፎውን በማጠናከር ውጤታማ የግብርና ሥራ እያከናወነ መሆኑንም ኃላፊው ገልጸዋል።
በመስክ ምልከታው ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣አርሶ አደሮች እና የግብርና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

