በወረዳው ከተረጂነት አስተሳሰብ ለመላቀቅ እና ምርታማ ለመሆን በተግባር የሚገለፅ ውጤት እየተመዘገበ ነው፦አቶ ሂካ አንበሳ
******
ጥቅምት 29/2018 ዓ/ም
በወምበራ ወረዳ ከተረጂነት አስተሳሰብ ለመላቀቅ እና ምርታማ ለመሆን የአመራሩና የህብረተሰቡ በተግባር የሚገለፅ ውጤት እየተመዘገበ እንደሚገኝ በመተከል ዞን የወምበራ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሂካ አንበሳ ተናገሩ።
በወምበራ ወረዳ ግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ፅህፈት ቤት አዘጋጅነት የወረዳው ከፍተኛ አመራሮችና የተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት በወረዳው በበጎንዲና ሙዝ ቀበሌዎች ከተረጂነት ወደ ምርታማነት በሚል መሪ ሃሳብ ከተረጂነት አስተሳሰብ ለመላቀቅ ያለመ የመስክ ጉብኝት ተካሂዷል።
የመስክ ጉብኝቱን የመሩት የወምበራ ወረዳ ግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዲቢሳ ገመቹ እንዳሉት፦በተለያዩ ጊዜያት የሚከሰቱ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ተረጅነትና ልመናን ባህል በማድረግ ሲያስቸግሩን እንደነበር በማስታወስ ነገር ግን ከለውጡ ዓመታት ወዲህ ከተረጅነት ስነ- ልቦና በመውጣት በራስ አቅም አደጋን መቋቋም የሚያስችል ጠንካራ ቁመና ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
በ2017/2018 ዓ/ም በጀት ዓመት በበጎንዲና ሙዝ ቀበሌዎች ከተረጂነት ወደ ምርታማነት በሚል መሪ ሃሳብ 50 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለመሸፈን ታቅዶ 19 ሄክታር መሬት በማሽላ፣አኩሪ አተርና በሌሎችም ሰብሎች በመሸፈን ምርት ለመሰብሰብ ቅድመ ዝግጅት መጠናቁቁን የገለፁት አቶ ዲቢሳ ህብረተሰቡ ጠንካራ የስራ ባህልን በመገንባት ተፈጥሮ ያደለችንን ሃብትና ፀጋዎችን በመጠቀም በምግብ ራስን ከመቻል ባለፈ እንደ ወረዳ በምግብ ራስን ለመቻል፤የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት በመጨመር የምግብ ዋስትናውን ለማረጋገጥ፤የህብረተሰቡን ኑሮ ለማሻሻል እንደ ሀገር የውጭ እርዳታን ለማስቀረት ትኩረት አድርጎ መስራት ከሁላችንም ይጠበቃል ሲሉ አሳስበዋል።
በመስክ ጉብኝቱ በመገት የወምበራ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሂካ አንበሳ ባስተላለፉት መልዕክት፦በወረዳው ከተረጂነት ለመላቀቅ እና ምርታማ ለመሆን የአመራሩና ህብረተሰቡ በተግባር የሚገለፅ ውጤት እየተመዘገበ እንደሚገኝ በመግለፅ ከተረጅነት ለመላቀቅ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የተሻለ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል ።
በወምበራ ወረዳ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ድሪባ አበራ በበኩላቸው፦ህብረተሰቡን ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለማሸጋገር እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት ፍሬያማ በመሆናቸው ተጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸው ገልፀዋል።
የየቀበሌዎቹ አርሶ አደሮች በበኩላቸው፦በበጀት ዓመቱ የተለያዩ ሰብሎችን በዘር በመሸፈን ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር በሚደረገው ጉዞ የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ እንደሚገኙና ለልማት ቅድሚያ ሰጥተው እየሰሩ መሆናቸውን አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በመጨረሻም ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት በውጤት የታጀቡ እንዲኾኑ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ሞዴል አርሶ አደሮች፤የቀበሌ ግብርና ልማት ጣቢያ ኃላፊዎች፤የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል ወደ ልማትና ምርት ለገቡ የሰላም ተመላሾችና ለሌሎችም ባለ ድርሻ አካላት በወረዳው አስተዳደር በኩል የእውቅና ምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።
የወምበራ ወረዴ ኮሙኒኬሽን እንደዘገበው

