የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ባደረገላቸው የሙያና የግብዓት ድጋፍ ተስፋ ሰጪ የበጋ ስንዴ ማልማታቸውን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአሶሳ ዞን የአቡራሞ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ፡፡
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ዞን የአቡራሞ ወረዳ አርሶ አደሮች በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ዕገዛ ያለሙት የበጋ ስንዴ በመልካም ቁመና ላይ ይገኛል፡፡
የአርሶ አደሮቹን በመስኖ የለማ ስንዴ የጎበኙት የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ዘርፍ ምክትል ፕሬዝደንት አብዱልሙህሲን ሀሰን (ዶ/ር) ዩኒቨርሲቲው የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሻሻል በምርምር የታገዘ ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል፡፡
በተለይ በስንዴ ልማት ስራ የተሻሻሉ ዝርያዎችን በማቅረብና እና ሙያዊ ድጋፍ በማድረግ አርሶ አደሩ ውጤታማ እንዲሆን ዩኒቨርሲቲው እየሰራ መሆኑን በዩኒቨርሲቲው የግብርና ልማት ተመራማሪ አብዮት አበጀ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
የአቡራሞ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱለጢፍ አፉዲ የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የስንዴ ልማት ስራው ውጤታማ እንድሆን ላበረከተው የምርጥ ዘር፣ የማዳበሪያ፣ የስልጠናና ክትትል ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ አታላይ ደረጀ አርሶ አደሩ የሚያገኛቸውን በምርምር የታገዙ መልካም ተሞክሮዎች በማስፋት ውጤታማነቱ እንዲሻሻል እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በጀማል አህመድ
